አዲሰ አበባ ፣ መስከረም 15 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ) ባህር ማዶ ተሻግሮ ወደ ሌላ ሃገር የሚሄድ አንድ ኢትዮጵያዊ በበርካታ ቤተ ዘመድ ሲሸኝ ይስተዋላል።

በዚህም በርካታ አላስፈላጊ ወጭ ከማውጣት ባለፈ የእንቅልፍ ሰአትን መስዋዕት ያደርጋል ፤ በሽኝት ምክንያት ትናንት ማታ ያጡትን እንቅልፍ ለማካካስ ደግሞ ፤ በማግስቱ ከስራ ገበታ መቅረት ይከተላል።

ሁኔታው በበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በብዛት የሚስተዋል መሆኑንም ነው አስተያየት ሰጭዎች የሚናገሩት።

ይህ ደግሞ ከግለሰቡ አልፎ ምርታማነትን በመቀነስ ሃገርን መጉዳቱ አይቀርም ባይ ናቸው።

በየዕለቱ በርካታ ሸኝ እና ተቀባዮች የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በበኩሉ ፥ ለተለያዩ ኪሳራዎች እየተዳገረኩኝ ነው ይላል።

ድርጅቱ እንደሚለው በግለሰቦች የአጠቃቀም ጉድለት በንብረቶች ላይ በሚደርሱ ጉዳቶች እና የበረራ ሰአታቸውን በሚያስተጓጉሉ መንገደኞች ምክንያት ነው ለኪሳራ እየተዳረገ የሚገኘው።

አንድ ግለሰብ ለመሸኘት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በመምጣት ለተለያዩ ወጭዎች እንደሚዳረጉም ነው ፥ የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ የሚናገሩት።

በቁጥራቸው መብዛት ምክንያትም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግሮችን ይፈጥራሉ ነው ያሉት።

ሁኔታውን የታዘቡትም የድርጅቱን ቅሬታ ይጋራሉ ፤ እነርሱ እንደሚሉት ሁኔታው ቢስተካከል እና ቢታሰብበት መልካም ነው።

እንደ ሌሎች ሃገራት ለመሸኘትም ሆነ ለመቀበል አንድ ሰው ብቻ በመላክ ጊዜ እና ገንዘባችንን በአግባቡ እንጠቀም በማለት አቶ ወንድም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

በራሄል አበበ